የትራፊክ ደኅንነት ጉዳያችን አድሮ ቃሪያ ከርሞ ጥጃ ለምን ሆነ? . . . 7 ወሳኝ ነጥቦች

Written by  Thursday, 04 August 2016 03:50
Rate this item
(0 votes)

 

የትራፊክ ደኅንነት ጉዳያችን አድሮ ቃሪያ ከርሞ ጥጃ ለምን ሆነ? . . . 7 ወሳኝ ነጥቦች

Posted on May 30, 2013by Dawit Worku

 ዳዊት ወርቁ

ግንቦት 2005

እንደ የዓለም ጤና ተቋም (WHO) ወቅታዊ መረጃ ከሆነ፣ እስከ ዛሬ ድረስ በኢትዮጵያ በትራፊክ አደጋ ብቻ የተቀጠፈው ነፍስ ቁጥር

22,786 ደርሷል፡፡  ይህም ማለት በተለያዩ ምክንያት ከሚከሰተው ሞት ከመቶ 2.77% ሲሆን፣ አማካይ የሟቾቹ ዕድሜ 37.83 ነው፡፡ ሀገሪቱ በትራፊክ አደጋ ብዛትም ከዓለም 12 ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ (በነገራችን ላይ በድህነትም 12 ደረጃ ላይ ናት)

እንደ  ኦል አፍሪካን ዶትኮም ድረ ገጽ ከሆነ፣ በሀገራችን በየዓመቱ 2000 ሰዎች በመኪና አደጋ ህይወታቸውን ያጣሉ፡፡ 4-5 ሚሊየን ብር የሚሆን ጥፋትም በንብረትና ቁስ  ላይ እንደሚደርስ ይገመታል፡፡ 10 ተሽከርካሪዎች 160  ሰዎች ላይ የሞት አደጋ ሲከሰት፣ ባደጉት አገሮች ግን 2 እና 3 ሰው ብቻ ይሆናል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ በዋነኝነት የትራፊክ አደጋ የሚከሰው

1.       በአሽከርካሪዎች ብቃት ማነስ (Inefficient of drivers)

2.      የሌሊት ጉዞ (Night Travel)

3.      ጫት ቅሞና አልኮል ጠጥቶ በማሽከርከር (deriving Under the Influence of Khat & Alcohol)

4.      ከፍጥነት በላይ በማሽከርከር (Over Speeding)

5.       ደህንነታቸው አስጊ ደረጃ ላይ በደረሱ ተሽከርካሪዎች በመገልገል (Poor vehicle technical fitness) ዋነኞቹ ምክንያቶች ናቸው፡፡

ሚዲያዎች ሁሉ፣ በተለይም FM ራዲዮኖቻችን ቢያንስ በቀን ለአንድ ጊዜ ያህል  በመንገድ ትራፊክ ደኅንነት ዙሪያ አንዳች ነገር ሳይሉ ውለው አድረው አያውቁም፡፡ ይሁንና፣ ጉዳዩ ባለበት ቦታ እየረገጠ ይመስላል፡፡ ፈቅ የሚል ነገር ጨርሶ አይታይም፡፡ ሁሉ ውይይት፣ ሁሉ ልፈፋ፣ ሁሉ የትምህርት ጋጋታ ውኃ እየበላው ይመስላል፡፡ በመንገድ ትራፊክ አደጋ የሚጎዳውም ሰው ከዕለት ዕለት እየጨመረ ነው፡፡

ለመሆኑ ለምንድነው በትራፊክ ጉዳያችን ላይ ሥር ነቀል የሆነ ለውጥ ማምጣት ያልታቻለውና አደጋውን መቀነስ ያልተቻለው? . . . ዕነሆ ሰባት ወሳኝ ነጥቦች፣

1.  የአንድ ሰሞን ርብርብ

በትራፊክ ጉዳዮቻችን ላይ ሥር ነቀል ለውጥ ማምጣት ያልተቻለው አደጋውም ከዕለት ወደዕለት እየከፋና እያደገ የሄደበት የመጀመሪያው ምክንያት፣ ምንም እንኳ ህግ አውጪዎቹና አጽዳቂዎቹ ተስማምተው፣ አሜን ብለው ህግና ደንቡን ቢቀርጹም፣ ማስተግበሩና አስተግባሪዎቹ ግንጉድ አንድ ሰሞን ነውእንዲሉ፣ የአንድ ሰሞን ጉዳይ በመሆናቸው ነው፡፡ ለምሳሌ፡- ያለዜብራማቋረጫ ያቋረጠ እግረኛ እንዲህና እንዲያ ይደርጋል፣ ይባልና ለአንድ ሰሞን ምድረ ትራፊክ ፖሊስ ተብዬ ሁላ በዘመቻ ታጥቆ ይነሳል፣ ከዚያም ለጥቂት ቀናት ወጧ እንዳማረላት ባልቴት ጉድጉድ ካሉ በኋላ ሁሉንም ነገር እንዳለፈ ውኃ ይረሱታል፡፡

ትርፍ መጫን ከዚህ በኋላ በፍጹም አይፈቀድምበተባለ ማግሥት፣ ትርፍ ሰው ሳይሆን ችቦ የጫኑ የሚመስሉ ሃይገሮችና ተሳፋሪውን እንደአሻንጉሊት የሚቆጥሩት የአዲስ አበባ ሚኒባስ ታክሲ፣ ሾፌሮች ለቀናት ያህል ከትራፊክ ፖሊሶች ጋር የአይጥና ድመት እንካ ሰላንቲያቸውን ከተጫወቱ በኋላ፣ ሁሉም ነገር ወደ ቀድሞው ፍሰቱ ይቀጥላል፡፡

የመኪኖች አካላት ደኅንነት ሁናቴ፣ የመንጃ ፈቃድ ትክክለኛነት፣ የአሽከርካሪ ብቃት፣ ቀበቶ፣ ወዘተ . . . ለአንድ ሰሞን ክትትል ከተደረገባቸው በኋላ ሁሉም ነገር ወደ ቀድሞው ልምምድ ይመለሳል፡፡ ስለዚህ የትራፊክ ደኅንነታችን አድሮ ቃሪያ፣ ከርሞ ጥጃ የመሆኑ ጉዳይ ቁጥጥሩና ክትትሉ የአንድ ሰሞን ጉዳይ ስለሆነ ነው ብል አልተሳሳትኩም፡፡

2.  መንጃ ፈቃድ

ብዙዎችሹፍርናኮ የመሃይም ሥራ ነውይላሉ፡፡ አባባሉ ለብዙ ጊዜያት አይገባኝም ነበር፣ በኋላ ነው እውነታው የተገለጠልኝ፡፡ ለካስ መንጃ ፈቃድ ለማውጣት ብር እንጂ ዕውቀት እምብዛም ፋይዳ የለውምና፡፡

እኛ አገር የመንጃ ፈቃድ ለመያዝ ዋነኛው ነገር ዳጎስ ያለ ብር ነው፡፡ ዕውቀት ሁለተኛ ነገር ነው፡፡

የአውሮኘላን አብራሪ ለመሆን ግን ብር ሳይሆን ዕውቀት አስፈላጊ ነው፡፡ ለዚያውም በእንግሊዘኛ፣ በሒሳብና ፊዚክስ ትምህርቶች ሰቃይ ተማሪ መሆን ይጠበቃል፡፡ ግና አውሮፕላንም የሰው ስሪት ነው፤ መኪናም የሰው እጅ ስራ ነው፡፡ አውሮፕላንም የሰው ነፍስ ይዞ ነው የሚጓዘው፣ መኪናም እንደዚያው፡፡ ታዲያ ለመኪናስ የአውሮፕላኑን ያህል ባይሆንም፣ ነገሩ የህይወት ጉዳይ ነው ተብሎ ለምን አልተካበደም ?. . .  የመኪና ቁጥር ከአውሮፕላን ቁጥር ስለሚልቅ ይሆን? . . . ወይስ የመኪና ከአውሮፕላን ዋጋ ሲነጻጸር ምንም ስለሆነ? . . . ነው ወይንስ ሌላ የማላውቀው ምክንያት ይኖር ይሆን?

3. ጫትና አልኮል

 ሌላኛው ምክንያት ጫትና አልኮል በመጠቀም የሚያሽከረክሩ ሰዎች ላይ ቁጥጥሩ በመላላቱ ነው፡፡ በተለይም ከምሽት ክለባትና ጭፈራ ቤቶች ተዝናንተው መሪ የሚጨብጡ ሰዎች፣ በሰው ላይ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ የኅብረተሰቡ መገልገያዎች ላይ እያደረሱ ያሉት ጉዳት ይህ ነው አይባልም፡፡ የኤሌክትሪክ ምሰሶዎች፣ የድልድይ ብረቶች፣ የትራፊክ ደኅንነት ምልክቶች፣ ወዘተ . . . አልኮልና ዕፅ ያደነዘዛቸው አሽከርካሪዎች ሰለባ ናቸው፡፡

ከዚህ ሁሉ ባሻገር ግን በአገራችን የትራፊክ ሲስተም ከተሰወሰነ ፍጥነት በላይ እና ጠጥተው ለሚያሽከረክሩ ሰዎች የራዳር መቆጣጠሪያ (radar guns)  እጥረት ወይም ከነጭራሹ አለመኖር ሌላው ተያይዞ የሚነሳ ደጋፊ ምክንያት ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ የአዲስ አበባ ከተማንና የክልል ከተሞችን የሚያማክልኮምፒዩተራይዝድ ኔትዎርኪንግአለመኖርም ችግሩን አብሶታል፡፡

4.  የሌት ጉዞ  

አራተኛው ምክንያት ሌሊት ሌሊት በሚጓዙ መኪኖች ላይ ቁጥጥር ማዕቀብ ባለመጣሉ ነው፡፡ በተለይም በዘልማድአባዱላየሚባሉት መኪኖች በአንድ ጉዞ ብቻ ከመነሻው ተነስተው መድረሻው ላይ መገኘት በመፈለጋቸው አደጋውን የከፋ አድርገውታል፡፡

አንድ ሰው መነሻውን አዲስ አበባ አድርጎ በፈለገበት አቅጣጫ ቢጓዝ፣ ፈንግል እንዳያዛት ዶሮ በየሰርጡና በየጉድባው፣ እዚህም እዚያም መኪኖች ተፈንግለው ቢያይ አይደንቅም፡፡

5.  የአሽከርካሪዎች ብስለት

 አምስተኛው ምክንያት፣ በአእምሯቸውና ዕድሜያቸው ያልበሰሉ ጨቅላ አሽከርካሪዎችመሪን ያህል ነገር በመጨበጣቸው ነው፡፡ በተለይም ከወላጆቻቸው መኪና ሰርቀው፣ ሰው አየኝ አላየኝ እያሉ በፍርሃትና በችኮላ እየተርበተበቱ የሚነዱ ልጆች አደጋውን እያባሱት ይገኛሉ፡፡

6.  ቅጥ ያጣ ድህነት

 ስድስተኛውና አንኳሩ ምክንያት መላቅጡን ያጣው ድህነታችን ነው፡፡ በትራንስፖርት እጥረት እንደ ሰርዲን ታጭቆ የሚጓዘው ህዝባችን ደግሞ የችግሩ ገፈት ቀማሽ ነው፡፡

አንድ የመኪና ካምፖኒ መኪና ሲፈበርክ የጭነቱን ልክ ይወስናል፡፡ ማለት በሌላ አነጋገር ጭነቱ ከዚህ ካለፈ መኪናው አደጋ ላይ ነው ማለት ነው፡፡ ይሁንና በኛው አገር ራሱ የመንገድ ትራንስፖርት ባለሥልጣን የሻረው በሚመስለው ህጉ በተለይም በሃይገር ባሶች ላይ ይህ ነው የማይባል ሥፍር ቁጥር የሌላቸው ተሳፋሪዎች ታጭቀው ሲታይአቤቱ ሰውረን ከመዓቱየሚለው ጸሎት ትውስ ይላል፡፡

7.  ሙስና

በትራፊክ ጉዳያችን ላይ ሥር ነቀል የሆነ ለውጥ ማምጣት ያልታቻለውና አደጋውን መቀነስ ያልተቻለው ሰባተኛው ምክንያት ሙስና ነው፡፡

ብዙ ሰዎች በተለይም ኪሳቸው የሚናገር፣ ብዙ ውጣ ውረድ ሳያዩ መንጃ ፈቃዱ ተሠርቶ ቤታቸው ድረስ ሊመጣላቸው ይችላል፡፡ በዚህ አጋጣሚ የፀረ ሙስና መርማሪ ኮሚሽን በነካ እጁወደ መንገድ ትራንስፖርት ባለሥልጣን /ቤት ጐራ ቢል አትርፎ የሚወጣ ይመስለኛል፡፡

 

በአጠቃላይ ያልተፈታው የትራፊክ ደኅንነት ጉዳያችን በሕይወት፣ አካልና ንብረት ላይ ብቻ ሳይሆን የሚያደርሰው ሥነልቡናዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ቀውሱ የትየለሌ ነውና ጉዳዩ ጆሮ ዳባ ልበስ አይባልበትም፡፡

Seyfu Mekonen

Seyfu Mekonen is a founder and administrator of ethiosafety.com. As a founder and administrator he is responsible for free and up to date safety and security informations. He can be reached: seyfu2002@yahoo.com

You are here: Home Our Blog የትራፊክ ደኅንነት ጉዳያችን አድሮ ቃሪያ ከርሞ ጥጃ ለምን ሆነ? . . . 7 ወሳኝ ነጥቦች