የትራፊክ ጥሰቶችና ቅጣቶች

Written by  Saturday, 21 November 2015 00:44
Rate this item
(1 Vote)

ደንብ ቁጥር 27/2002 የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንገድ ትራፊክ ደህንነት ደንብ

በአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ቅ/መ/ቤት የተዘጋጀ

ታህሳስ 2002

በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በመንገድ ትራፊክ አደጋ ምክንያት በሰው ህይወትና ንብረት እንዲሁም በከተማው መስተዳድር ኢኮኖሚ ላይ ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ የመጣው የጉዳት መጠን አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን በመገንዘብ፣ ከአለም የቴክኖሎጂ ዕድገት ጋር ተያይዞ በተሽከርካሪዎች  ምክንያት ለአደጋ የሚያጋልጡ ሁኔታዎችን ለመቆጣጠር የህግ ማእቀፍ ሊኖር ስለሚገባ ከዚህ ቀደም በወጡ የትራፊክ ደህንነት ደንቦች ውስጥ ያልተካተቱና አዳዲስ የጥፋት አይነቶች እየተከሰቱ በመምጣታቸው የተነሳ አሁን ከደረስንበት የዕድገት ደረጃ ጋር የሚጣጣም ዘመናዊ የትራፊክ ስርአትን የተከተለ ደንብ ማውጣት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ በተሻሻለው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቻርተር አዋጅ ቁጥር 361/1995 አንቀጽ 23(1) (ረ) መሰረት የከተማው አስተዳደር ካቢኔ ይህንን ደንብ አውጥቷል፡፡

የመጀመሪያ የቅጣት እርከን (ብር 60.00)

የጥፋት ዓይነቶች

1.   ተሽከርካሪን ያለአግባብ የጎተተ

2.   በመንገድ ላይ እንስሳት የነዳ

3.   የተሟላ የጭነት ማቀፊያ (ስፖንዳ) የሌለው ተሽከርካሪ የነዳ

4.   የጥሩንባ ድምጽ ያለአግባብ (በማይገባ ቦታ) ያሰማ

5.   ተገቢ ባለልሆነ የጥሩንባ ድምጽ የተጠቀመ

6.   በትርፍ ጭነት ላይ ምልክት ያላደረገ

7.   ከፍተኛ ጭስ የሚያጨስ ተሽከርካሪ የነዳ 

8.   የለማጅ ምልክት ሳይለጠፍ ተሽከርካሪ መንዳት ያስተማረ

9.   ባልተወሰነ ቦታ ተሽከርካሪ መንዳት ያስተማረ

10. ባልተወሰነ ሰዓት ተሽከርካሪ መንዳት ያስተማረ

11. ለሃዘን ከሆነ ሳያስፈቅድ ወይም ተክሎ ወዲያውኑ በአቅራቢያው ላለው የፖሊስ ጣቢያ ሳያሳውቅ ድንኳን በመንግድ ላይ ያቆመ

12. መንገድ ላይ ተሽከርካሪ ያሳጠበ

13. ለእግረኛ ክልክል ነው የሚል ምልክት ባለበት መንገድ ወይም ለእግረኛ በተከለከለ የማሳለጫ መንገድ ያቋረጠ እግረኛ  

14. ለእግረኛ ማቋረጥ ከተፈቀደው ውጪ በቀለበት መንገድ ወይም በሌላ መንገድ ያቋረጠ እግረኛ

15. ለእግረኛ ተከልክሎ በታጠረ መንገድ ያቋረጠ እግረኛ 

16. ለእግረኛ የተዘጋጀ መንገድ እያለ ከዚያ ውጪ በተሽከርካሪ መንገድ ላይ የተጓዘ እግረኛ

17. በመንገድ ላይ የንግድ ሥራ የሠራ

18. የመጀመሪያ ህክምና ኪት በተሽከርካሪው ያልያዘ

19. ውሃ በእግረኛ ላይ የረጨ

20. በመንገድ ላይ በግጭትና በብልሽት ምክንያት የወደቁ የተሽከርካሪ ስብርባሪ ያላጸዳ

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

የሁለተኛ የቅጣት እርከን (ብር 80.00)

የጥፋት ዓይነቶች

 

1.   ወደማይሄድበት አቅጣጫ ምልክት ያሳየ

2.   ምልክት ሳያሳይ ተሽከርካሪን ከቆመበት ቦታ ያንቀሳቀሰ ወይም ያቆመ

3.   በተሽከርካሪ የውጪ አካል ላይ ሰው የጫነ

4.   የቀስት አቅጣጫ የለቀቀ

5.   የቀኙን ጠርዝ ሳይዝ በዝግታ የነዳ

6.   ያለአግባብ ወደኋላ ያሽከረከረ

7.   ለአላፊ ተሽከርካሪ ቅድሚያ የከለከለ

8.   በተከለከለ ቦታ ላይ ተሽከርካሪ ያቆመ

9.   በትራፊክ ደሴት ላይ ተሽከርካሪ ያቆመ

10. በድልድይ ላይ ተሽከርካሪ ያቆመ

11. በትራፊክ ምልክት አጠገብ ተሽከርካሪ ያቆመ

12. በትራፊክ መብራት አጠገብ ተሽከርካሪ ያቆመ

13. በባቡር ሀዲድ አጠገብ ተገቢውን ጥንቃቄ ያላደረገ

14. መብራት እያለው በማብሪያ ጊዜ ሳያበራ ያሽከረከረ

15. የመንጃ ፈቃድ /የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ሳይዝ ያሽከረከረ

16. የመንጃ ፈቃድ/የአሽከርካሪነት ብቃት ማረጋገጫ በወቅቱ ያላሳደሰ

17. ያለፍቃድ ተሽከርካሪ መንዳት ያስተማረ

18. ሠሌዳው የተደመሰሰ ወይም የተቆረጠ ወይም የተሸፈነ ተሽከርካሪ ያሽከረከረ

19. ከተፈቀደው ፍጥነት በታች ያሽከረከረ 

20. በእጅ የሚገፋ ወይም የሚሳብ ጋሪ በዋና መንገድ ላይ የገፋ ወይም የሳበ

21. የጉዞ መስመር ጠብቆ ያላሽከረከረ

 

ሦስተኛ የቅጣት እርከን (ብር 100.00)

የጥፋት ዓይነቶች

 

1.   በ25 ሜትር ርቀት ምልክት ሳያሳይ የተሽከርካሪውን አቅጣጫ የቀየረ

2.   የሚከለክል ምልክት የጣሰ

3.   የሚያስገድድ ምልክት የጣሰ

4.   ደሴት በግራ ያቋረጠ

5.   በጠባብ መንገድ ላይ ያቆመ

6.   በመታጠፊያ መንገድ ላይ ያቆመ

7.   የመንገድ አከፋፋይ ደሴት/መስመር/ ያቋረጠ

8.   የጭንቅላት መከላከያ/ሄልሜት/ ሳያደርግ ሞተር ሳይክል ያሽከረከረ ወይም ከኋላ ሰው ያፈናጠጠ

9.   የተበላሸ ተሽከርካሪ መንገድ ላይ የጠገነ

10. ከተወሰነለት መቀመጫ ወይም የጭነት ልክ በላይ የጫነ

11. በተሽከርካሪው ላይ የተጫነውን ጭነት በሚገባ ያላሰረ ወይም ያላለበሰ

12. ሳይፈቀድ እይታን የሚከለክሉ መጋረጃዎች ወይም ተለጣፊ ላስቲክ የለጠፈ

13. አፈር፣አሸዋ ድንጋይ የመሳሰሉትን ባልተፈቀደ ቦታ ላይ ያራገፈ ወይም እንዲራገፍ ያደረገ

14. ሌሎች የትራፊክ ፍሰትን የሚያሰናክሉ ድርጊቶችን የፈፀመ

15. በተሽከርካሪው ላይ ተገቢ ያልሆነ አካል የጨመረ

16. የተለጣፊ ምልክት /ቦሎ/ያለጠፈ

17. የአሽከርካሪው ዕይታ የሚከለክል ማንኛውንም አይነት ማስታወቂያ ወይም ሌላ ነገር መንገድ ዳር ወይም መሀል ላይ የተከለ

18. ለተለያዩ ተግባራት መንገድ ቆፍሮ ወደነበረበት ሳይመልስ የቀረ

 

 

አራተኛ የቅጣት እርከን (ብር 120.00)

የጥፋት ዓይነቶች

 

1.   ተሽከርካሪ በእንቅስቃሴ ላይ እያለ ተሳፋሪ የጫነ ወይም ያወረደ

2.   በተሽከርካሪ መግቢያ ወይም መውጫ በር ላይ ያቆመ

3.   አመታዊ የተሽከርካሪ ደህንነት ምርመራ ያላደረገ

4.   ግልፅ ጉድለት ያለው ተሽከርካሪ ያሽከረከረ

5.   ባልተሟላ መብራት ያሽከረከረ

6.   ተሽከርካሪ ደርቦ ያቆመ

7.   የሚታጠፍበትን አቅጣጫ ሳይዝ ያሽከረከረ

8.   በትራፊክ ደሴት ላይ ያሽከረከረ

9.   ከተማ ውስጥ ከባድ መብራት /ባውዛ/ የተጠቀመ

10. ያለማንፀባረቂያ ምልክት የተበላሻ ተሽከርካሪን በመንገድ ላያ ያቆመ

11. ከ2 ሰዓት በላይ ከባድ ተሽከርካሪ በመንገድ ላይ ያቆመ

12. በሰንሰለት የሚሽከረከርና በሰአት ከ10 ኪ.ሜ በታች የሚጓዝ ልዩ ተሽከርካሪ መንገድ ላይ ያሽከረከረ

13. በአውቶብስ ማቆሚያ ስፍራ ላይ ሌላ ተሽከርካሪ ያቆመ

14. ከባድ ተሽከርካሪ ላይ ከኋላ አንፀባራቂ ምልክት ሳያሳይ ያሽከረከረ

 

አምስተኛ የቅጣት እርከን (ብር 140.00)

የጥፋት ዓይነቶች

 

1.   ደረጃውን ባልጠበቀ መንጃ ፈቃድ (የአሽከርካሪነት ብቃት ማረጋገጫ) ያሽከረከረ

2.   መስቀልኛ መንገድ ላይ ቅድሚያ ያልሰጠ

3.   ቅድሚያ መስጠት ሲገባው የከለከለ

4.   የትራፊክ መብራት ወደ ቀኝ መታጠፍ ለሚፈቅድለት ተሽከርካሪ መንገድ የዘጋ

5.   አለአግባብ ተሽከርካሪ የቀደመ

6.   የተሽከርካሪን በር ከፍቶ ያሽከረከረ

7.   በሕግ ከተወሰነው ከፍታ፣ርዝመት ወይም ስፋት ውጪ ጭነት የጫነ

8.   የእግረኛ መንገድ ያለፍቃድ የከለለ፣ ያጠረ ወይም ያሳጠረ

9.   የእግረኛ መንገድ ለተለየ አገልግሎት ያዋለ

10. ከሀዘን በስተቀር ያለፖሊስ  ፈቃድ በመንገድ ላይ ድንኳን የተከለ

11. የፖሊስ ወይም በጎ ፈቃደኛ ትእዛዝ ያልፈፀመ

12. ዕድሚያቸው ከሰባት አመት በታች የሆኑ ህፃናትን በተሽከርካሪው ጋቢና አሳፍሮ ያሽከረከረ

13. ህጋዊ ስልጣን ካለው አካል ፈቃድ ሳያገኝ በመንገድ ትራፊክ ምልክት የተጠቀመ

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

ስድስተኛ የቅጣት እርከን (ብር 160.00)

(ከባድ  ትራፊክ  ደንብ  ጥፋት)

የጥፋት ዓይነቶች

 

1.   ሰክሮ፣ አደንዛዥ ዕፅ ወይም ጫት ወይም ሺሻ አጭሶ ያሽከረከረ

2.   የጆሮ ማዳመጫ (ኤርፎን) ጆሮው ውስጥ በመክተት ሬድዮ እያዳመጠ ወይም ሞባይል እያናገረ ያሽከረከረ

3.   ሞባይል ስልክ በእጁ ይዞ ወይም ተሽከርካሪው ላይ ገጥሞ እያናገረ ማንኛውንም አይነት ተሽከርካሪ ያሽከረከረ

4.   የተሽከርካሪ የመቀመጫ ቀበቶ ሳያስር ወይም ሌሎች እንዲያስሩ  ሳያደርግ ያሽከረከረ

5.   ሬዲዮ፣ ቴፕ፣ሲዲ በከፍተኛ ድምጽ ከፍቶ እያዳመጠ ያሽከረከረ

6.   የመንጃ ፈቃድ/የአሽከርካሪነት ብቃት ማረጋገጫ/ሳይኖረው ያሽከረከረ

7.   የመንጃ ፈቃድ/የአሽከርካሪነት ብቃት ማረጋገጫ/ ለሌለው ሰው እንዲያሽከረክር የሰጠ

8.   ለእግረኛ ቅድሚያ ያልሰጠ

9.   ቀይ የትራፊክ መብራት የጣሰ

10. በህግ ከተወሰነው ፍጥነት በላይ  ያሽከረከረ

11. የእሳት አደጋ መከላከያ  ተሽከርካሪ ውሃ መሙያ ቦታ ላይ ተሽከርካሪ ያቆመ

12. ለአደጋ አገልግሎት ተሽከርካሪ ቅድሚያ ያልሰጠ

13. በእሳት አደጋ ወይም ሆስፒታል በር ላይ ተሽከርካሪ ያቆመ

14. በእግረኛ መንገድ ላይ ተሽከርካሪ ያቆመ

15. በእግረኛ ማቋረጫ ላይ ተሽከርካሪ ያቆመ

16. ምንም መብራት ሳይኖረው ያሽከረከረ

17. በተከለከለ መንገድ ወይም አቅጣጫ ያሽከረከረ

18. በሐል መንገድ ላይ ተሳፋሪ ወይም ጭነት የጫነ ወይም ያወረደ

19. የትራፊክ አደጋ ፈፅሞ ቦታው ላይ ያልቆመ

20. ቴሌቪዥን ወይም ቪዲዮ እያየ ያሽከረከረ

21. የትራፊክ መብራት ላይ ወይም በመስቀልኛ መንገድ ላይ ወይም ሌላ ማናቸውም መንገድ ላይ በልመና ላይ ለተሰማሩ ሰዎች ገንዘብ ያሰጠ ወይም የሰጠ ወይም ማንኛውም አይነት ግብይት ያደረገ ወይም ያስደረገ 

22. የመንገድ ትራፊክ ምልክት ያበላሸ፣ የሚያስተላልፈውን ይዘት የቀየረ ወይም ከተተከለበት ቦታ ያዞረ ወይም በመንገድ ምልክት ላይ ማስታወቂያ የለጠፈ

23. ተሽከርካሪን ከተፈቀደለት አገልግሎት ውጪ ለሌላ አገልግሎት የተጠቀመ

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

ሰባተኛ የቅጣት እርከን

(እጅግ ከባድ የትራፊክ ደንብ ጥፋት)

የጥፋት ዓይነቶች

 

7.1 በብር 300.00 የሚያስቀጡ ጥፋቶች

ሀ. በቂ ርቀት ሳይኖር በማሽከርከር በንብረት ላይ ጉዳት ያደረሰ

ለ. ያለአግባብ ተሽከርካሪን ወደኋላ በማሽከርከር በንብረት ላይ ጉዳት ያደረሰ

7.2 በብር 350.00 የሚያስቀጡ ጥፋቶች

ሀ. ተሽከርካሪን ከቆመበት ያለጥንቃቄ ሲያነሳ በንብረት ላይ ጉዳት ያደረሰ

ለ. ተሽከርካሪን ደርቦ ሲታጠፍ በንብረት ላይ ጉዳት ያደረሰ

ሐ. ተሽከርካሪን በመገልበጥ በራሱ ንብረት ላይ ጉዳት ያደረሰ

7.3 በብር 400.00 የሚያስቀጡ ጥፋቶች

ሀ. የተሽከርካሪውን መሪ ያለአግባብ ተጠቅሞ  በንብረት ላይ ጉዳት ያደረሰ

ለ. ከመጋቢ መንገድ አቅጣጫ ተሽከርካሪን እያሽከረከረ ወጥቶ በንብረት ላይ ጉዳት ያደረሰ

ሐ. ተሽከርካሪን እያሽከረከረ ከመንገድ ወጥቶ በንብረት ላይ ጉዳት ያደረሰ

መ. ለሌላ ተሽከርካሪ በተገቢው ቦታ ላይ ቅድሚያ በመከልከል በንብረት ላይ ጉዳት ያደረሰ

ሠ. ተሽከርካሪ እያሽከረከረ በቀኝ በኩል በመቅደም በንብረት ላይ ጉዳት ያደረሰ

ረ. ያለደረጃ የተሽከርካሪነት ብቃት ማረጋገጫ ይዞ በማሽከርከር  በንብረት ላይ ጉዳት ያደረሰ

ሰ. የአደጋ ተካፋይ ሆኖ ያመለጠ ወይም ወደሚመለከተው አካል ያልቀረበ

7.4 በብር 500.00 የሚያስቀጡ ጥፋቶች

ሀ. ከተፈቀደለት ፍጥነት በላይ በማሽከርከር  በንብረት ላይ ጉዳት ያደረሰ

ለ. የሚያስገድድ የሚያስጠነቅቅ የሚከለክል ወይም ሌላ በመንገድ ላይ የሰፈረ የትራፊክ ምልክት ወይም ማመልከቻ በመጣስ በንብረት ላይ ጉዳት ያደረሰ

ሐ. በህግ ከተፈቀደው ከፍታ  ርዝመት ወይም ስፋት በላይ ተሽከርካሪው ላይ ጭኖ በማሽከርከር በንብረት ላይ ጉዳት ያደረሰ

መ. ግራ መንገድ ውስጥ ገብቶ  እያሽከረከረ በንብረት ላይ ጉዳት ያደረሰ

ሠ. አደንዛዥ ፅ ወይም መጠጥ ጠጥቶ በማሽከርከር በንብረት ላይ ጉዳት ያደረሰ

ረ. የቴክኒክ ጉድለት ያለበትን ተሽከርካሪ በማሽከርከር በንብረት ላይ ጉዳት ያደረሰ

 

 

 

 

 

7.5 በብር 700.00 የሚያስቀጡ ጥፋቶች

ሀ. የቴክኒክ ጉድለት ያለበትን ተሽከርካሪ የትራፊክ ምልክትና ማመልከቻ ጥሶ በማሽከርከር በንብረት ላይ ጉዳት ያደረሰ

ለ. የቴክኒክ ጉድለት ያለበትን ተሽከርካሪ በመጠጥ ወይም በአደንዛዥ ፅ ሰክሮ በማሽከርከር በንብረት ላይ ጉዳት ያደረሰ

ሐ. መንጃ ፈቃድ ሳይኖረው ተሽከርካሪ በማሽከርከር በንብረት ላይ ጉዳት ያደረሰ

መ. ተሽከርካሪ እያሽከረከረ በንብረትም ሆነ በሰው ላይ አደጋ አድርሶ ያመለጠ

ሠ.  ለአንቡላንስ ወይም ለእሳት አደጋ ተሽከርካሪ ቅድሚያ ከልክሎ በማሽከርከር በንብረት ላይ ጉዳት ያደረሰ

1. የግል ተሽከርካሪ አሽከርካሪ

 

1.1   ከሁለት ጊዜ በላይ ከባድ ወይም እጅግ ከባድ የትራፊክ ደንብ ጥፋት የፈፀመ ከገንዘብ ቅጣቱ በተጨማሪ የመንጃ ፈቃዱ ወይም የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ፈቃዱ ተይዞ፡-

1.   ለ3ኛ የጥፋት ሪከርድ ለ3 ወር ተሽከርካሪ እንዳያሽከረክር ይታገዳል

2.   ለ4ኛ የጥፋት ሪከርድ ለ6 ወር ተሽከርካሪ እንዳያሽከረክር ይታገዳል

3.   ለ5ኛ የጥፋት ሪከርድ ለ1 ዓመት ተሽከርካሪ እንዳያሽከረክር ይታገዳል

4.   ለ6ኛ የጥፋት ሪከርድ ለ2 ዓመት ተሽከርካሪ እንዳያሽከረክር ይታገዳል

5.   ለ7ኛ የጥፋት ሪከርድ የመንጃ ፈቃዱ /አሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ፈቃዱ/ ውድቅ ይሆናል፡፡ ሆኖም ከ3 ዓመት በኋላ አዲስ መንጃ ፈቃድ ሊያወጣ ይችላል፡፡

 

1.2    ከ5 ጊዜ በላይ ማንኛውንም የትራፊክ ደንብ ጥፋት የፈፀመ ከንዘብ ቅጣቱ  በተጨማሪ የመንጃ ፈቃዱ ወይም የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ፈቃዱ ተይዞ፡-

1.   ለ6ኛ የጥፋት ሪከርድ የመንገድ ሥነ-ሥርአት ፈተና በድጋሚ እንዲወስድ ይደረጋል፡፡

2.   ለ7ኛ የጥፋት ሪከርድ የመሰናክል ፈተና በድጋሚ እንዲወስድ ይደረጋል፡፡

3.   ለ8ኛ የጥፋት ሪከርድ የከተማ ውስጥ ማሽከርከር ፈተና በድጋሚ እንዲወስድ ይደረጋል፡፡

አባሪ ለ

የሪከርድና ቅጣት ሠንጠረዥ

 

2.  የሌላ ተሽከርካሪ አሽከርካሪ

 

2.1  ከ3 ጊዜ በላይ ከባድ ወይም እጅግ ከባድ የትራፊክ ደንብ ጥፋት የፈፀመ ከገንዘብ ቅጣቱ በተጨማሪ የመንጃ ፈቃዱ ወይም የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ፈቃዱ ተይዞ፡-

1.   ለ4ኛ የጥፋት ሪከርድ ለ6 ወር ተሽከርካሪ እንዳያሽከረክር ይታገዳል

2.   ለ5ኛ የጥፋት ሪከርድ ለ1 ዓመት ተሽከርካሪ እንዳያሽከረክር ይታገዳል

3.   ለ6ኛ የጥፋት ሪከርድ ለ2 ዓመት ተሽከርካሪ እንዳያሽከረክር ይታገዳል

4.   ለ7ኛ የጥፋት ሪከርድ የመንጃ ፈቃድ ወይም የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ፈቃዱ  ውድቅ ይሆናል፣ ሆኖም ከ5 ዓመት በኋላ አዲስ መንጃ ፈቃድ ሊያወጣ ይችላል፡፡

5.    ለ8ኛ የጥፋት ሪከርድ የመንጃ ፈቃዱ ወይም የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ፈቃዱ ይሰረዛል፡፡

 

2.2  ከ7 ጊዜ በላይ ማንኛውንም የትራፊክ ደንብ ጥፋት የፈፀመ ከገንዘብ ቅጣቱ በተጨማሪ የመንጃ ፈቃዱ ተይዞ፡-

 

1.   ለ8ኛ የጥፋት ሪከርድ በድጋሚ የመንገድ ሥነ-ሥርአት ፈተና እንዲወስድ ይደረጋል፡፡

2.   ለ9ኛ የጥፋት ሪከርድ የመሰናክል ፈተና በድጋሚ እንዲወስድ ይደረጋል፡፡

3.   ለ10ኛ የጥፋት ሪከርድ የከተማ ውስጥ ማሽከርከር ፈተና በድጋሚ እንዲወስድ ይደረጋል፡፡

4.   ለ11ኛ የጥፋት ሪከርድ የመንጃ ፈቃድ /የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ፈቃዱ/ ውድቅ ይሆናል፣ ሆኖም ከ1 ዓመት በኋላ አዲስ መንጃ ፈቃድ ሊያወጣ ይችላል፡፡

ይህንን ደንብ ለማስፈፀም እንዲቻል በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንገድ ትራፊክ ደህንነት ቁጥር 27/2002 አንቀፅ /10/ ንዑስ አንቀፅ /2/ መሰረት የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቅርንጫፍ መስሪያ ቤት ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ከደንብ ማስከበር አገልግሎትና ሌሎች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመመካከር ይህንን የአፈፃፀም መመሪያ አውጥቷል፡፡

ክፍል አንድ

ጠቅላላ

1.  አጭር ርዕስ፡-

 

ይህ መመሪያ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንገድ ትራፊክ ደህንነት ደንብን ለማስፈፀም የወጣ መመሪያ ቁጥር 1/2002 ዓ.ም ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል፡፡

 

2.  አውጪው መሥሪያ ቤት፡-

 

የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቅርንጫፍ መስሪያ ቤት በአዲስ አበባ ከተማ የመንገድ ትራፊክ ደንብ ቁጥር 27/2002 አንቀጽ /10/ ንዑስ /2/ መሠረት ይህንን መመሪያ አውጥተዋል፡፡

 

3.  ዓላማ፡-

 

የአፈፃፀም መመሪያ የሚከተሉ አላማዎች አሉት፡፡

 

1.   በከተማው በአሽከርካሪዎች፣ በእግረኞች እና በእንስሳት ምክንያት በየእለቱ በሰውና በንብረት ላይ የሚደርሰውን የትራፊክ አደጋ መቆጣጠርና  መከላከል፡፡

 

2.   የተገልጋዩን ሕዝብና የአሽከርካሪን ጥቅም ደህንነትና ንብረት ለማስጠበቅ ፍትሃዊ የሆነ አገልግሎት እንዲያገኙ ለማድረግና የተቀላጠፈ የአሰራር ስርአቱን በጠበቀ የአገልግሎት አሰጣጥ ሕዝብ እርካታ እንዲያገኝ ማድረግ፡፡

 

3.   በአሽከርካሪዎች፣ እግረኞች እንዲሁም እንስሳት ዝውውር ዘመናዊ የመንገድ አጠቃቀም ስርአትን ማስፈን፡፡

 

4.   የመንገድ ላይ ትራፊክ አደጋዎችና መንስኤዎቻቸው መግታት ወይም መቀነስ፡-

 

4.ትርጓሜ፡-

 

የቃሉ አግባብ ሌላ ትርጉም የሚያሰጠው ከሆነ በስተቀር በዚህ መመሪያ ውስጥ፡-

1.   ‹‹ከተማ›› ማለት የአዲስ አበባ ከተማ ነው፡፡

2.   ‹‹ከተማ አስተዳደር››ማለት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር

3.   ‹‹የእግረኛ መንገድ›› ማለት ተሽከርካሪዎች እንዲንቀሳቀስበት ከተዘጋጀው መንገድ ጠርዝ ተከትሎ ለእግረኛ እንቅስቃሴ የሚውል መንገድ ነው፡፡

4.   ‹‹የእግረኛ ማቋረጫ›› ማለት እግረኞች አቋርጠው እንዲያልፉበት ተብሎ በመንገድ ላይ ምልክት የተደረገበት የመንገድ ክፍል ወይም በቀለበት መንገድ ላይ የተሰራ ድልድይ ነው፡፡

 

5.   ‹‹የትራፊክ ተቆጣጣሪ›› ማለት ዩኒፎርም የለበሰ ሆኖ ለትራፊክ ቁጥጥር በኮሚሽኑ የተመደበ የፖሊሲ ሰራዊት አባል ወይም በጎ ፈቃድ ነው፡፡

 

6.   ‹‹ተሳፋሪ›› ማለት በቤት አውቶሞቢል  ለሕዝብ አገልግሎት የሚሰጡ ሌሎች  ተሽከርካሪዎች ውስጥ ተገቢውን ክፍያ ከፍሎ ወይንም ሳይከፍል የሚጓዝ መንገደኛ ወይም ተጓዥ ሰው ነው፡፡

 

7.   ‹‹አሽከርካሪ›› ማለት ጋሪ፣ሰረገላ፣ ብስክሌት፣ባለ ሞተር ተሽከርካሪ የቤት አውቶሞቢል፣ ግማሽ ተሳቢና ተሳቢውን ጨምሮ የሚያሽከረክር ሰው ነው፡፡

 

8.   ‹‹አስፈፃሚ አካል›› ማለት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንገድ ትራፊክ ደንብ ቁጥር 27/2002 ዓ.ም በአንቀጽ 11 የተመለከተ ይሆናል፡፡

 

9.   ‹‹ደንብ›› ማለት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንገድ ትራፊክ ደህንነት ደንብ ቁጥር 27/2002 ዓ.ም ነው፡፡

 

5.  የዚህ መመሪያ የተፈፃሚ ወሰን

 

1.   ይህ መመሪያ ተፈፃሚ የሚሆነው በአዲስ አበባ ከተማ ክልል ውስጥ በማናቸውም ትራፊክ እንቅስቃሴ ባለበት ቦታ ወይም መቆሚያ ስፍራ ላይ ሁሉ ነው፡፡

 

2.   እግረኛ መንቀሳቀሻም ሆነ ማቋረጫ በአግባቡ ባልተዘጋጀባቸው ስፍራዎችም እንዲሁም እህልና ሌሎች ዕቃዎችን በአህያ ጭነው በመንገድ ላይ የሚጓጓዙትን በሚመለከት ላልተወሰነ ጊዜ ተፈፃሚ አይሆንም፡፡

 

ክፍል ሁለት

 

6.  በአሽከርካረዎች በእግረኛውና በእንስሳት ባለቤቶች ላይ ስለሚደረግ ቅጣት አፈፃፀም

 

1.   የቅጣት ማሳወቂያ ፎርም የተሰጠው አሽከርካሪ ቅጣቱን ለቅርንጫፍ መ/ቤቱ ወይም በቅርንጫፍ መ/ቤቱ ውክልና ፈቃድ ተሰጥቶ በሚሰበስብ ተቋም በ48 ሰአት ውስጥ መክፈል ይኖርበታል፡፡

 

2.   እንስሳት የተያዙባቸው  አጥፊዎች ክፍል ፈፅመው እንስሳቱን ሲረከቡ በአግባቡ በተሽከርካሪ ጭነው ማንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል፡፡

 

3.    ትራፊክ  ፖሊሶች  በዝርዝር የተቀመጡ ጥፋቶች በነጠላ  ወይም በአንድነት ለመፈፀም አሽከርካሪ መንጃ ፈቃድ በመቀበል የክስ ቻርጅ በትክክል ሞልተው መስጠት አለባቸው፡፡

 

4.   በትራፊክ ደንብ መተላለፍ የክስ ቻርጅ ተቀብሎ በ30 ቀናት ውስጥ ቀርቦ ካልፈፀመ ቀድሞ በተመዘገበበት ሪከርድ ላይ ሁለት ነጥብ ተደምሮ ይመዘገብበታል፡፡

 

5.   በትራፊክ ደንብ መተላለፍ የክስ ቻርጅ ተቀብሎ በ31-40 ባሉት ቀናት ውስጥ ቅጣቱን ያልፈፀመ አሽከርካሪ ቀድሞ በተመዘገበበት ሪከርድ ነጥብ ላይ 4 ነጥብ ተደምሮ ይመዘገብበታል፡፡

 

6.   በትራፊክ ደንብ በመተላለፍ የክስ ቻርጅ ተቀብሎ ቀድሞ ሳይፈፅም ከ40 ቀናት በላይ የሆነውን አሽከርካሪ ለ3 ወር መንጃ ፈቃዱ ይታገዳል፡፡ በተጨማሪም 4 ነጥብ ሪከርድ ይመዘገብበታል፡፡

 

7.   የትራፊክ ደንብ በመተላለፍ የክስ ቻርጅ ተቀብሎ ቅጣቱን ሳይፈፅም ተሽከርካሪ ሲነዳ የተገኘ አሽከርካሪ ይቆምና በድጋሚ መንጃ ፈቃድ ሳይዝ በማሽከርከር መጥሪያ ይሰጠዋል፡፡

 

 

 

7.የአሽከርካሪ ግዴታዎች ስለሚጣልባቸው ቅጣቶች

1. ማንኛውም አሽከርካሪ ጫት ወይም ሌላ አደንዛዥ ዕፅ ወስዷል ተብሎ የሚገመተው በሚያሽከረክረው ተሽከርካሪ ውስጥ ተሳፋሪ የሆነ ሰው ለንግድ ተግባር ከጫነው ውጭ ጫት ወይም ዕፁ የተገኘ ወይም ሲጠቀም የተገኘ እንደሆነ ነው፡፡

2. በሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ አገልግሎት የሚሰጥ ረዳት ጫት ወይም አደንዛዥ ዕፅ ወስዶ ወይም እየወሰደ በተሽከርካሪው ላይ አገልግሎት መስጠት የተከለከለ ነው፡፡

3. የትራፊክ ፖሊስ በማንኛውም ጊዜ አደንዛዥ ዕፅ ወይም ጫት አሽከርካሪው ወይም ረዳቱ ስለወሰዱ ወይም በተሽከርካሪው ውስጥ ስለመኖሩ በቂ ጥርጣሬ ሲኖረው ተሽከርካሪ አስቁሞ ሊፈትሽ ወይም ሊያጣራ ይችላል፡፡

4. የትራፊክ ፖሊስ አንድ አሽከርካሪ አደንዛዥ ዕፅ ወይም አልኮል መጠጥ የወሰደ ስለመሆኑ ገሃድ በወጣ ሁኔታ ወይም በቂ በሆነ ምክንያት ሲጠረጠር አሽከርካሪውን አስቁሞ ሊመረምርና ሊያጣራ ይችላል፡፡

5. ማንኛውም አሽከርካሪ በመጠጥ ሰክሯል ማለት የሚቻለው በዚሁ ተግባር በተሰራው መሳሪያ ሲመረመር ከፍተኛ የአልኮል መጠኑ በደሙ ውስጥ 0.80 ሚሊ ግራም በላይ ወይም በሚያስወጣው ትንፋሽ ውስጥ 0.40 ሚሊ ግራም በሊትር ንፁህ አልኮል በልጦ ሲገኝ ነው፡፡

6. በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 5 የተገለጸው መሳሪያ ተግባራዊ እስከሚሆን ድረስ የትራፊክ ፖሊስ አልኮል በጠጥ ወይም አደንዛዥ ዕፅ አንድ አሽከርካሪ ወስዶ ማሽከርከሩን በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 4 መሰረት ያጣራል፣ አደንዛዥ ዕፅ ወይም አልኮል በጠጥ አሽከርካሪው መውሰዱ ሲያረጋግጥ ተገቢውን እርምጃ ይወስዳል፡፡

7. ጊዜ ያለፈበት የእለትና ተላላፊ ሰሌዳ ለጥፎ የሚያሽከረክር አሽከርካሪ ሲገኝ ተገቢውን ሰሌዳ ወይም ማስረጃ እስኪያቀርብ ድረስ ተሽከርካሪው በትራፊክ ፖሊስ ተይዞ ለ72 ሰአት ይቆያል፡፡ በ72 ሰአት ጊዜ ውስጥ ሰሌዳውን ወይም ማስረጃውን አቅርቦ አሽከርካሪውን ካልተረከበ ተሽከርካሪውን እንዳልፈለገ ተቆጥሮ የዚህ መመሪያ አግባብነት ያላቸው ድንጋጌዎች ተፈፃሚ ይሆናል፡፡

8. በደንቡ መሰረት እግረኛ ላይ ቅጣት የሚፈፀመው የደንብ መተላለፍ የተፈፀመው

1.   ለእግረኛ ማቋረጫ ድልድይ ወይም እግረኛ መንቀሳቀሻ መንገድ በተዘጋጀበት የቀለበት መንገድ ላይ ወይም፣

 

2.   ለእግረኛ መንቀሳቀሻ መንገድ በአግባቡ ተለይቶለትና ተዘጋጅቶ ባለበት በየትኛውም የከተማው መንገድ ወይም፣

 

3.   ለእግረኛ ማቋረጫ የተዘጋጀና  ተገቢው ምልክት ባለበት በየትኛውም የከተማው መንገድ ላይ ሲሆን ነው፡፡

9. ቅጣት ስላልፈፀሙ እግረኞች

1.    ማንኛውም እግረኛ በደንቡ መሰረት የተቀመጠውን  የገንዘብ ቅጣት ለመክፈል ፈቃደኛ ካልሆነ ለ24 ሰአታት በማረፊያ ቤት እንዲቆይ ይደረጋል፡፡

2.    በዚህ አንቀጽ ለንዑስ አንቀጽ 1 አፈጻጸም የደንብ መተላለፍ በተፈጸመበት ቀበሌ ውስጥ ያለው ደንብ ማስከበር አገልግሎት እና የፖሊስ ጣቢያ በጋራ ሃላፊነት አለባቸው፡፡

3.    የቀበሌው የደንብ ማስከበር አገልግሎት ሰራተኛ ደንብ የተላለፈውን ወደ ፖሊስ ጣቢያ ያደርሳል፡፡ በዚህ ሂደት እግረኛው እንቢተኛ ሲሆን የፖሊስ ሃይል ይተባበራል፡፡

 

4.    መንገደኛው ማረፊያ ቤት ከገባ በኋላ ቅጣቱን የከፈለ እንደሆነ ገቢው ለቀበሌው ገቢዎች ጽ/ቤት በደረሰኝ ገቢ ይደረጋል፡፡

5.    በማረፊያ ቤት ቆይታ ጊዜ ውስጥ ቅጣቱን ለመክፈል ፈቃደኛ ያልሆነው መንገደኛ የማህበራዊ አገልግሎት ስራዎችን እንዲሰራ ይደረጋል፡፡

6.    በዚህ አንቀጽ ለንዑስ አንቀጽ 3 አፈጻጸም የማህበራዊ አገልግሎት ስራ ማለት መንገድ ዳርቻን ማጽዳት ፣ ለመንገድ ውበት የተተከሉ ዛፎችን መኮትኮት ወይም ውሃ ማጠጣት እና ተመሳሳይ ስርዎችን ነው፡፡

7.    የማህበራዊ አገልግሎት ስራን ተፈፃሚ ለማድረግ የጽዳት ውበታና መናፈሻ አገልግሎት ጽ/ቤት ተገቢውን ቁሳቁስ በማዘጋጀት ያቀርባል፡፡

 

10. ቅጣት ስላልፈፀሙ የእንስሳት ባለቤቶች

 

1.   ማንኛውም ሰው መንገድ ላይ የእንስሳት ንግድ ሲያካሄድ የተገኘ ወይም የትራፊክ እንቅስቃሴ  በሚገድብ ሁኔታ እንስሳትን ከቦታ ቦታ ሲያዘዋውር የተገኘ እንደሆነ የቀበሌ ደንብ አስከባሪ ወዲያውኑ እንስሳቱን በመያዝ ለከተማ ግብርና ልማት ለዚሁ አላማ ወደ ተዘጋጀለት የእንስሳት ማቆያ ለ48 ሰአት እንዲቆይ ይደረጋል፡፡

 

2.    ጥፋተኛው ሰው የተያዘበትን እንስሳ በደንቡ እርከን አንድ መሰረት ቅጣቱን ፈጽሞ እንስሳውን ካላስለቀቀ እንስሳው በጨረታ ተሸጦ የቅጣት ገንዘቡን እንስሳው ወደማረፊያ የተወሰደበትን ትራንስፖርት ማጓጓዣ ለእንስሳቱ ማቆያ ጥበቃ የወጣው ወጪ ተቀንሶ ቀሪው ገንዘብ ለባለቤቱ ይመለሳል፡፡

 

3.   ለእንስሳት ማቆያ ቦታ እንዲሁም ተገቢውን መኖ የከተማ ግብርና ጽ/ቤት ያዘጋጃል፡፡

 

4.   የእንስሳው ሽያጭ የሚከናወነው ደንብ መተላለፍ ከተፈፀመበት ቀበሌ የደንብ ማስከበር አገልግሎት፣ የከተማ ግብርና ጽ/ቤት፣ የቀበሌው አስተዳደር ፖሊስና ፋይናንስ ጽ/ቤት የተውጣጣ አምስት አባላት በያዘ ኮሚቴ አማካይነት ይሆናል፡፡

 

5.   የኮሚቴው ሰብሳቢ ከፋይናንስ ጽ/ቤት የሚወከለው ሰው ይሆናል፡፡

 

6.   ከእንስሳት ሽያጭ የሚገኘው ገቢ ለቀበሌው ገቢዎች ጽ/ቤት በመንግስት ገቢ አሰባሰብ ስርአት መሰረት ገቢ ይደረጋል፡፡

 

7.   ከሽያጩ ተገቢው የመንግስት ገቢ ተቀንሶ የሚተርፈውና ለእንስሳው ባለቤት ተመላሽ የሚደረገውን ባለቤቱ ቀርቦ ካልተረከበ ከሽያጩ ጊዜ ጀምሮ ለሶስት ወራት በአደራ እንዲቀመጥ ይደረጋል፡፡

 

8.   በሦስት ወራት ጊዜ ውስጥ ቀርቦ ባለቤቱ ካልወሰደ እንዳልፈለገ ተቆጥሮ ገንዘቡ ለመንግስት ፈሰስ ይደራጋል፡፡

 

9.   በዚህ ደንብ ለአንቀጽ 10 አፈጻጸም የሚሸጠው እንስሳ ወጪዎችን በሚሸፍን መጠን ብቻ ሆኖ ከዚያ በላይ ያለው እንስሳ ለባለቤቱ ይመለሳል፡፡

 

 

 

 

 

 

 

 

11. ቅጣት ስላልፈፀሙ ተሽከርካሪዎች

1.   በደንቡ አንቀጽ 6 ንዑስ አንቀጽ 2 መሰረት የቅጣት ከንዘብ ያልተከፈለ ሲሆንና ተሽከርካሪው የሚሸጥ ሲሆን የዚህ መመሪያ አንቀጽ 10 አግባብነት ያላቸው ድንጋጌዎች ተፈጻሚ ይሆናል፡፡

 

2.   የቅጣት ፎርም ተሰጥቶ በጊዜው ቀርቦ ቅጣት ያልከፈለ አሽከርካሪን የመንገድ ትራንስፖርት ቅርንጫፍ መስሪያ ቤት እና ፖሊስ ኮሚሽን ዝርዝራቸውን በማስታወቂያ ሰሌዳቸው ላይ በመለጠፍ በአስር የስራ ቀናት ውስጥ ቀርቦ ቅጣቱን እንዲፈፅም ሁለት ጊዜ ያወጣሉ፡፡

 

3.   የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቅርንጫፍ መስሪያ ቤት እና ፖሊስ ኮሚሽን በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 2 አፈፃፀም ተገቢውን መረጃ በወቅቱ ይለዋወጣሉ፡፡

12. ስለሪከርድ ነጥብ አሰጣጥ

1.   የመንገድ ትራፊክ ደህንነት ደንብን ለማስፈፀም የትራፊክ ፖሊስ ተቆጣጣሪ ለአሽከርካሪዎች በፈፀሙት ጥፋት መጠን የቅጣት ሪከርድ ነጥብ ይሰጣቸዋል፡፡

 

2.   በጠቅላላው ሪከርድ 28 ነጥቦች ሲኖሩት የሪከርድ ነጥብ አሰጣጡም እንደሚከተለው ይሆናል፡፡

ሀ/ በደንቡ አንደኛ እርከን ስር በተቀመጡት

   የጥፋት ዓይነቶች አንድ ነጥብ ይሰጣል፣

ለ/ በደንቡ ሁለተኛ እርከን ስር በተቀመጡት

   የጥፋት ዓይነቶች ሁለት ነጥብ ይሰጣል፣

ሐ/ በደንቡ ሦስተኛ እርከን ስር በተቀመጡት

   የጥፋት ዓይነቶች ሦስት ነጥብ ይሰጣል፣

መ/ በደንቡ አራተኛ እርከን ስር በተቀመጡት

    የጥፋት ዓይነቶች አራት ነጥብ ይሰጣል፣

ሠ/ በደንቡ አምስተኛ እርከን ስር በተቀመጡት

    የጥፋት ዓይነቶች አምስት ነጥብ ይሰጣል፣

ረ/ በደንቡ ስድስተኛ እርከን ስር በተቀመጡት

    የጥፋት ዓይነቶች ስድስት ነጥብ ይሰጣል፣

ሰ/ በደንቡ ሰባተኛ እርከን ስር በተቀመጡት

    የጥፋት ዓይነቶች ሰባት ነጥብ ይሰጣል፣

አሽከርካሪው በተለያየ ወቅት ደንብ በተላለፈ ቁጥር የሚመዘገብበት ነጥብ እየተደመረ በመሄድ 28 ነጥብ ሲደርስ በተቀመጠው ደንብ መሰረት የመጨረሻው የቅጣት አይነት ይፈፀምበታል፡፡

 

 

 

 

ክፍል ሦስት

የሪከርድ ነጥብን ስለመመዝገብ የቅጣት አፈፃፀሙ ሁኔታ

13. የሪከርድ ነጥብን ስለመመዝገብ

መጀመሪያ ጊዜ በደንብ መተላለፍ የተከሰሰ አሽከርካሪ ከገንዘብ ቅጣቱ በተጨማሪ ለእርከኑ የተሰጠው ነጥብ ይመዘገባል፡፡

1.   በየጊዜው የትራፊክ ደንብን በመተላለፍ  የሚከሰሱ አሽከርካሪዎች  መረጃ በመንገድ ትራንስፖርት ቅርንጫፍ መ/ቤት አማካኝነት በኮምፒዩተር ተመዝግቦ ይያዛል፡፡

 

2.   አሽከርካሪው በተደጋጋሚ በፈፀማቸው ጥፋቶች ጠቅላላ ድምሩ 16-18 ነጥብ ሲደርስ ለሶስት ወር ተሽከርካሪ እንዳያሽከረክር  ይታገዳል፣

 

3.   አሽከርካሪው በተደጋጋሚ በፈፀማቸው ጥፋቶች ጠቅላላ ድምሩ 19-21 ነጥብ ሲደርስ የብቃት ማረጋገጫ መንጃ ፈቃዱ ለስድስት ወር እንዲታገድ ይደረጋል፡፡

 

4.   አሽከርካሪው በተደጋጋሚ በፈፀማቸው ጥፋቶች ጠቅላላ ድምሩ 22-26 ነጥብ ሲደርስ የብቃት ማረጋገጫ መንጃ ፈቃዱ ለአንድ ዓመት እንዲታገድ ይደረጋል፡፡ ከእገዳው በተጨማሪ ሁለተኛ ደረጃ ተሃድሶ/ትምህርት ስልጠና/ይወስዳል፡፡

 

5.   አሽከርካሪው በተደጋጋሚ በፈፀማቸው ጥፋቶች ጠቅላላ ድምሩ 27 ነጥብ ሲደርስ የብቃት ማረጋገጫ መንጃ ፈቃዱ ለሁለት ዓመት እንዲታገድ ይደረጋል፡፡ ከእገዳው በተጨማሪ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ተሃድሶ/ትምህርት ስልጠና/ይወስዳል፡፡

 

6.   አሽከርካሪው በተደጋጋሚ በፈፀማቸው ጥፋቶች ጠቅላላ ድምሩ 28 ነጥብ ወይም     ከዚያ በላይ ሲደርስ የብቃት ማረጋገጫ መንጃ ፈቃድ ሊያወጣ ይችላል፡፡

14. መመሪያ ስለማሻሻል እና ተፈፃሚነት

የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቅርንጫፍ መ/ቤት እንደ አስፈላጊነቱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመመካከር ይህን መመሪያ ሊሻሻል ይችላል፡፡

ይህን መመሪያ ከታህሳስ 26 ቀን 2002 ዓ.ም ጀምሮ ተፈፃሚ ይሆናል፡፡

የአዲስ አበባ ትራንስፖርት

 

ቅርንጫፍ መ/ቤት

Seyfu Mekonen

Seyfu Mekonen is a founder and administrator of ethiosafety.com. As a founder and administrator he is responsible for free and up to date safety and security informations. He can be reached: seyfu2002@yahoo.com

You are here: Home Safety Driving safety የትራፊክ ጥሰቶችና ቅጣቶች