አደጋና ደህንነት

Written by  Monday, 23 March 2015 04:31
Rate this item
(0 votes)

አደጋና ደህንነት

 

ስለ አደጋ እንዲህ ነው ተብሎ የሚወጣለት ታሪካዊ ትንታኔ ወይም ጥናታዊ ዘገባ ባይኖርም  በየእለት እንቅስቃሲያችን አብሮን የሚኖር ኣንደኛው የሕይወታችን አካል ነው፡፡

ሠው ለመኖር መብላት፣ መጠጣት፣ መተንፈስ፣ መስራት፣ መተኛት፣ መነሳት እንደሚያስፈልገው ሁሉ በነዚህ ሁላ ተፈጥሯዊ ሂደቶች ውስጥ እንደ ሳንካ ወይም እንቅፋት በመሆን ህይወቱን ሲያጠለሽበት ይኖራል፡፡

ለመኖር ሲባል የሚበላው ምግብ ሰውነታችንን አወፍሮ ወይም መርዞ ወይም አንቆ ወይም ደግሞ ቧጦ ለጉዳት ብሎም እስከ ሞት ያደረሰበት አጋጣሚ ብዙ ነው፡፡

አደጋ ድንገቲ ቢሆንም ብዙ ጥንቃቄ ከተደረገበት ድንገተኛነቱ አይኖርም፡፡ መጠጥ በልኩ ከተጠጣ ለጤና ተስማሚ፣ ለመንፈስ አርኪ የሚሆነውን ያክል አብዝቶ ከተጠጣ ደግሞ በድንገት አዙሮ ያደፋል፣ አቅልን ያስታል፡፡ ለግጭት ይዳርጋል፣ ከዚያም አልፎ ተርፎ ለአካል ጉዳትና ሞትንም ያመጣል፡፡

እንግዲህ አደጋ ድንገተኛነቱን ይተውና ባለማሰብ ባለማመዛዘን ሰው ጎትቶ የሚያመጣው ሆኖ ያርፈዋል፡፡

ተው አትዝለል ትሰበራለህ፣ ተው አትብላው የተመረዘ ነው፣ ተው አትንካ ዘሎ ይመታሃል ሲባል "አይ እኔንማ እንዴት" ? ፣ ይቺነች ደግሞ የምታቅተኝ ? ብሎ ወዶ በፈቃዱ ገብቶበት እግሩ የተሰበረውን አይኑ የጠፋውን፣ አፉ የተጣመመውን ሁሉ በድንገተኛ አደጋ እንዲህ ሆነ ለማለት ያስቸግራል፡፡

ድንገተኛ በራሱ የራሱ ተግባርና ኃላፊነት ያለው እንጂ ማንም እያወቀ፣ እያየ፣ ተው እየተባለ ዘሎ የገባበትን ሁሉ "በድንገተኛ"ለማለት ይከብዳል፡፡

ያለእውቀት፣ ያለዝግጅት፣ ይህን ያደርሳል ተብሎ ሳይገመት፣ የመጣን ድንገቲ ከደፋሩና ከቀባጩ ጋር መደመር መልካም ፍርድ አይመስለኝም፡፡

አንድ ሰው በሁለት እግሩ ሁለት ዛፍ ሲወጣ ሰይጣን ያየውና ‹‹ አይ ይሄ ሰው አሁን ቢወድቅ እኮ በኔ ሊያሳብብ ነው›› አለው ይባላል፡፡

እናም ድንገተኛው በራሱ ከመጣ የተለተለውን ተልትሎ የጠቀለለውን ጠቅልሎ የገጨውንም አጋድሞ ያጋደመውን አንከባሎ፣ያንከባለለውንም ከአፈር ለውሶ የሆነውን እንደልሆነ፣ የተደረውን እንዳልተደረገ ፡ የረዘመውን አሳጥሮ የተሰቀለውን አውርዶ ሹልክ ብሎ እንደመጣ ሾልኮ ይሄዳል፡፡

 እኔ ዛሪ ብእሬን እንዳነሳ ያስገደደኝ ለእንዲህ ዓይነቱ ድንገቲ ሳይሆን ህግ ወጥቶለት ስርዓት ተበጅቶለት፣ አታድርግ የሚለውን ህግ ጥሶ ወይም በእንዝህላልነት በቸልተኝነት ህጉን ሳይከተል ስህተት ውስጥ ገብቶ የሚዳክረውን ጠቆም ለማድረግ ነው፡፡

 በትራንስፖርት ህግ ጠጥቶ መንዳት አስነዋሪም አሳፋሪም  ሆኖ ቅጣት የተበጀለት ህግ የተቀረፀለት ነው፡፡ ሰው ለምን ጠጣ አይባልም፡ ጠጥቶ ማሽከርከር ግን ህጉን መተላለፍ ነው፡፡ ህጉ መፍረሱ በራሱ የሚያስቀጣ ነው ፣ ተጠጥቶ መነዳቱ ህጉ እንዳልተከበረ የሚያሳይ ነው። ሊሎች ህጎች ራሳቸውን ችለው ሲቆሙ ይህ ግን ደጋፊ እንኩዋን ያጣ ሆኖኣል። አሽከርካሪው በመጠጥ መንፈስ አደጋ እንደሚደርስ፣ የሰው ህይወትና ንብረት እንደሚጠፉ እያወቀ ንብረት እንደሚወድም እየተገነዘበ ሆን ብሎ ወይም ኣውቆ (ሰፊ የማሰቢያ የማመዛዘኛ ጊዚ እያለው) በቸልተኝነት ወይም በግዴለሽነት መኪና እየነዳ ጉዳት ሊፈፅም የሕዝብ ሰላም ሊያውክ እየተጓዘ ነውና ጉዳቱን ከማድረሱ በፊት ከተያዘ 'በመግደል ሙከራ ወንጀል'! ህጉ በሚደነግገው መሠረት ሊጠየቅ ይገባዋል፡፡  ኣደጋው ደርሶ ከሆነም የአደጋው ልክ ታውቆ የሚጠየቅበት ቢሆንም በመጀመሪያ ደረጃ ግን ይህ አደጋ ሳይደርስ በፊት በነበረው እንቅስቃሲው ሕጉ ሊጠነክርበት ይገባል።  አደጋው ከደረሰ በኋላ ያለው እንደተጨማሪ ሆኖ በራሱ ግን በመጠጣቱና በማሽከርከሩ ብቻ ህጉ ሊከብድበት ግድ ነው፡፡

 በዓለማችን በአብዛኛው የመኪና አደጋ የሚደርሰው ጠጥቶ ከመንዳት ጋር በተያያዘ ነው፡፡ ከሃገራችን ህግ በስተቀር በሌላው ዓለም ጠጥቶ ሲያሽከረክር የተገኘ በመጀመሪያ መኪናውን ይቀማል፣ በሁለተኛ ደረጃ ከአንድ ዓመት በላይ የሚደርስ የመንዳት እገዳ ይደነገግበታል፣ ከተደጋገመም ጭራሽ እንዳይነዳ ይወሰንበታል፡፡ ቆንጠጥ የሚያደርግም የገንዘብ ቅጣት ይጣልበታል፡፡ እንግዲህ እስሩ እንግልቱ መዋከቡና እርግጫው እንዳለ ሆኖ ነው፡፡ በዚያም ላይ እድሚ ልኩን የማይለቀው የመጥፎ ባህርይ የሁዋላ ታሪክ (ricord) እየተከተለው ነው። ስለዚህ በየጊዚው ከሚነሱ እንክርዳዶች በስተቀር ማንም ሰው እንደ ብረት የጠነከረውን ሕግ ፍራቻ ጠጥቶ ለመንዳት አይደፋፈርም።

 በሃገራችንስ፡- እንዳውም የተገላቢጦሽ ሆኖ እናገኘዋለን ብል አላጋነንኩም፡፡ የመጠጥ ግሮሠሪው ባለቤት ሾሬር ደንበኛውን እንደምንም አቅፎ መኪናው ውስጥ ሲያስቀምጠው በስነ ስርዓት እየነዳ እቤቱ የሚገባ ሠካራም የሠፈሬን ሰው አውቃለሁ፡፡ እንግዲህ ኣስቡ ጠንካራ ህግ ቢኖር ሾፊሩ ጠጥቶ ለመንዳት ባልተደፋፈረ፡ ባለግሮሰሪውም ተባባሪ ባልሆነ ነበር ።

 አሁን ላይ ሆኜ ሳስበው የግሮሰሪው ባለቤት ቢያንስ ለደንበኛው ቢጨነቅለት ቢያስብለት መልካም ነበር እላለሁ፡ ከጠጣ እንዳይነዳ ቢከለክለው ወይም በታክሲ ቢልከው የተሻለ እንደነበር እገምታለሁ፡፡ ያ ሰው አደጋ ቢደርስበት ወይም ቢሞት "የዛን እለት እንዲህ አድርጌው በነበር" እያለ በፀፀት የሚያልቀው እሱ ይመሰለኛል፡፡

 አትጠጡ እያልኩ አይደለም ያለሁት፡ ከጠጡ አይንዱ ነው፡፡ እንደሚነዱ  ካወቁ አይጠጡ፡ መጠጥ አንድ ብሎ ተጀምሮ እንደቀልድ ለስካር የሚያደርስ በመሆኑ መኪናዎን በያዙ እለት በፍፁም ላለመጠጣት ይወስኑ፡፡ ወደ መጠጥ አካባቢም አይቅረቡ ግድ ከሆነብዎ ደግሞ በመጀመሪያ የመኪናዎን ቁልፍ ከእጅዎ ያውጡ የማይጠጣው ጓደኛዎ እንዲነዳልዎ ያድርጉ፡፡ ያም ካልሆነ ታክሲ ወይም ሌላ አማራጭ ይጠቀሙ፡፡

 ይህችን እለት በዘዴ በማሳለፍዎ ምናልባት በእርስዎ ምክንያት ሊጠፉ የነበረውን የሰው ህይወት አድነዋል፡፡ በእርስዎ ስካር ምክንያት ሊወድምና ለአካል ጉዳት ሊያበቃ የነበረው አጋጣሚ ተወግዷል፡፡ እናም ድንገቲው  በእርስዎ አርቆ አሳቢነት፣ በእርስዎ ብልህነት፣ በእርስዎ መልካም ሰውነት ሊወገድ ችሏል፡፡

 አይጠራጠሩ ጠጥተው ከሚነዱ ሠዎች አብዛኛው የሚታይና የማይታይ አደጋ ያደርሳሉ፡፡ የአደጋው ትንሽነትና ትልቅነት እንጂ ከሚነዱት መኪና መኮርኮም ጀምሮ እስከ ትልቁ ውድመት ድረስ በየቀኑ ጉዳት ይደርሳል፡፡

 እርስዎም ጓደኛዎ ከጠጣ እንዳይነዳ ይምከሩ፣ ይከልክሉ፡፡ ቢያስቸግርዎ እንኳ ለፖሊስ በመንገር እንዲገደድ ያድርጉት፡፡ ያ ማለት ህይወቱን አተረፉለት ከአደጋ አዳኑት ማለት ነው፡፡ በዚህ ምክንያት የሚመጣውን የዛሬውን የእለት ፀብ አይመልከቱ፡ ነገ የሚያመሰግንዎ ቀን ይከሰታል፡፡ ሞኝ ከራሱ ብልህ ከሌላው ይማራልና፡፡

 ጠጥቶ በመንዳት ብቻ አይደለም በቢሮም ሆነ በፋብሪካ ወይም በግንባታ እንቅስቃሴ ይህ ድንገተኛ አደጋ ይኖራል፡፡

 ያለ አቅሙ ‹‹ ኧረ ሁለት ሆናችሁ ያዙት›› ሲባል የለም ይቺ እንዴት ታቅተኛለች  ብሎ ያነሳው ብረት ወገቡን ቆርጦት ተሽመድምዶ የቀረውን ቤቱ ይቁጠረው፡፡ ትላንት ብረት ሲያገላብጥ የዋለ ሰራተኛ ዛሬ ባዶ ካርቶን አንሳ ቢሉት ሊያዳግተው ይችላል፡፡ ምክንያቱም ሰውነቱ በትላንቱ ሥራ ተጎድቷልና ወይም ገና ያልተፍታታ አካል ይዞ ነው የቀረበው ወይም ሌላ፡፡

 ብዙ ጊዜ ዝነኝነትና ጉራ ለድንገተኛው አደጋ ይዳርጋል፡፡ ‹‹እሱ ደፋር ነው እሱ ያደርገዋል›› ሲባል አልችልም አይሆንልኝም ከማለት ይልቅ "እንዴት እንደዚህ ክበውኝ ራሴን አቀላለሁ" ብሎ ዘሎ አደጋ ውስጥ የሚገባ ብዙ ነው፡፡ " እሱ የታወቀ ነው፣ ባለዝና ባለክብር ነው" ሲባል ላት ወይም ባት ለማይሆነው ሽንገላ ተሸንፎ ኑሮውን ህይወቱን የሚጎዳና ሊነሳ በማይችልበት ውድቀት ገብቶ የሚዳክረውን ቤቱ ይቁጠረው፡፡ ይህም ድንገተኛ ይምሰል እንጂ በራሱ አደጋ ነው፡፡ በእርሱ ንዝህላልነት ቤተሠቡን ለችግር ለረሃብ ይዳርጋልና፡፡ በእርሱ ጉራ ቤተሠብ ይበተናልና፡፡

 እንግዲህ የድንገተኝነትና የአደጋ መልኩና ብዛቱ የትየለሌ ቢሆንም እኛ የእያንዳንዱዋን እርምጃችንን እንቅፋት ከመከላከል አንስቶ ነጥብ በነጥብ እየተከታተልን ኑሮን ጣእም እንዲኖረው ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡ ስናይ ዓይን የማይወጋውን፣ ስናሸት አፍንጫ የማይሰረስረውን፣ ስንራመድ የማያደናቅፈውን፣ ስንጨብጥ የማይኮሰኩሰውን፣ ስንበላ የማያስመልሰውን፣ ስንተኛ የማይጎረብጠውን፣ ስራ ስንሰራ ለጤናችን የተስማማውን፣ ስንናገር ሌላውን የማያስቀይመውን፣ ሌላም ሌላም መልካም መልካሙን እያደረግን ህይወታችንን አጣፍጠን በምድር የተወሰነልንን ጊዜ ጨርሰን እስክንሄድ ራሳችንን ጠብቀን በፍቅር መኖሩ መልካም ነው፡፡

" ክፉ ለራሱ ደግም ለራሱ" እንዲሉ መልካም መሆን በማንኛውም መስክ ስኬታማና ጤናማ ኑሮን ያመቻቻል፡፡ በተቃራኒው ከተሆነም ፀብ፣ ጭቅጭቅን ሠላም መደፍረሰን አደጋን ብሎም ሞት ማፋጠንን ይጋብዛል፡፡

 ስለዚህ አደጋ የሚጀምረው ከራስ ባህርይ ይሆናል፡፡ ሁሌ ጠማማ ከሆነ፣ መራራ ባህርይ ከተላበሰ ሰው የላመ የጣመ መጠበቅ የዋህነት ነው። ብዙ ጊዜ ለአደጋም የሚጋለጡት የሰከነ መንፈስ የሌላቸው እኒሁ ወገኖች ይሆናሉ፡፡

 ስለዚህ ጥፋታቸው ከራሳቸው አልፎ ለሌላውም የተረፈ ይሆናል፡፡ በመሆኑም በማህበራዊ ህይወት ውስጥ አንዱ አንዱን እየመከረ፣ የፈጠነው ዘገምተኛውን እየጎተተ፣ ብርቱው ደካማውን እየደገፈ፣ ንቁው የተኛውን እየቀሰቀሰ፣ ለኑሮ ለህይወት እንዲመች እያደረጉ እያጣፈጡ እየገነቡ መጓዝ ብልህነት ነው፡፡ ደህንነት (ሴፍቲ) ከዚህ ይጀምራልና፡፡

ሰይፉ መኮንን 

Seyfu Mekonen

Seyfu Mekonen is a founder and administrator of ethiosafety.com. As a founder and administrator he is responsible for free and up to date safety and security informations. He can be reached: seyfu2002@yahoo.com

You are here: Home